News and Events

ጤና ጣቢያዎቹ አገልግሎት አሠጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ በመደረጉ ተጠቃሚ መሆን ችለናል ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ
2025-12-28 08:24:00
ጤና ጣቢያዎቹ አገልግሎት አሠጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ በመደረጉ ተጠቃሚ መሆን ችለናል ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ። ጫጫ፤ ታህሳስ 17 ቀን 2018 ዓ.ም (አጠወመኮ)፦ \"ጤና ጣቢያዎቹ አገልግሎት አሠጣጣቸውን እንዲያሻሽሉ በመደረጉ ተጠቃሚ መሆን ችለናል ሲሉ ነዋሪዎች ገለፁ። በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላና ጠራ ወረዳ የኮቱ ከተማ እና በደብረ ብርሃን ሪጂኦ ፖሊታን ጫጫ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የሁለቱ ጤና ጣቢያ ተጠቃሚ ግለሰቦች በተካሄደ የልምድ ልውውጥ ላይ ገልፀዋል። Collaborative Development organization /CDO/ የተባለ ልማታዊ ግብረ ሰናይ ድርጅት ከመንግስት ጋር በመተባበር በሁለቱ ከተሞች ጤና ጣቢያዎች የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የዜጎች ማህበራዊ ኃላፊነትን /ተጠያቂነትን መወጣት ላይ አተኩሮ ከአጋር ድርጅቶች፣ ከህብረተሰቡ እና ከተቋማቱ ጋር ለአንድ ዓመት ሲሰራ ቆይቷል፤ የተነሳሳ፣ ብቃት ያለው፣ ርህራሄ የተሞላበት አገልግሎት ሰጪ ባለሙያ እንዲፈጠር እና የጤና አገልግሎቱ ቀልጣፋ የቆይታ ጊዜ እንዲኖረው፤ በጤና ተቋማቱ የመድሃኒት፣ የመመርመሪያ መሳሪያዎች ሌሎች ግብዓቶች እና የመሰረተ ልማቶች በሚሟሉበት ሁኔታዎች፤ የአንቡላንስ መኖር፣ አገልግሎት አሰጣጥ፣ አስተዳደርና ቁጥጥር እንዲሁም የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ ግቢዎች ውብ፣ ሳቢ፣ ማራኪ እና ምቹ እንዲሆኑ ዜጎች በተቌማቱ የእኔነት የኃላፊነት ስሜት እንዲኖራቸው እንዲጠይቁና እንዲሳተፉ ድርጅቱ ከመንግስት ጋር በትብብር በመስራት ለውጥ ማምጣት መቻሉ ተጠቁሟል፤ ይህንኑ መሰረት በማድረግም ከተቌማቱና ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት የተከናወኑ ተግባራትን እና የመጡ ለውጦችን ሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶችንና የመንግስት አካላትን በመጋበዝ የልምድ ልውውጥ እንዲቀሰምባቸው በኮቱ ጤና ጣቢያ የመስክ ምልከታ ተደርጓል። በመስክ ምልከታው ተጠቃሚ ነዋሪዎቹ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም በተቌማቱ አገልግሎት አሰጣጡ እንግልት የበዛበት፣ የባለሙያ ተነሳሽነት የሌለበት፣ መድሃኒት ከውጭ ግዙ የሚባልበት፣ መመርመሪያ መሳሪያ ባለመሟላቱ ሪፈር መባልና ለወጪ መዳረግ የበዛበት፤ እንዲሁም በብልሽት ምክንያት የአንቡላንስ አገልግሎት መቌረጥ እና የግቢ መሰረተ ልማት አለመሟላት ለአካል ጉዳተኞችና ለህሙማን እንቅስቃሴ ምቹ ያለመሆን ችግሮች ያሉባቸው ነበሩ ብለው፤ የእኔነት የኃላፊነት ስሜት እንዲኖረን እንድንጠይቅና እንድንሳተፍ በመደረጉ በመመካከርና በመነጋገር የነበሩ ችግሮች እንዲቀረፉ በማድረግ ተጠቃሚ መሆን ችለናል ሲሉ ገልፀዋል። በመስክ ምልከታው የተሳተፉ ያነጋገርናቸው የተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅት አካላት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ያደረገ ተጨባጭ ልምድ ልንቀስምበት የሚችል ስራ የተመለከትን ሲሆን በቀጣይም ተግባሩ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምክረ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል። የአንጎለላና ጠራ ወረዳ ጤና ጥበቃ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አከበረኝ የምሩ ገለፃ ከድርጅቱ ጋር ተቀናጅተን በመስራት የነበሩ ችግሮችን በመፍታት ህብረተሰባችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እና ሌሎች ልምድ እንዲቀስሙ ማድረግ ችለናል ብለዋል። የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪና ገቢዎች ኃላፉ አቶ ዮርዲያኖስ ተከስተ በበኩላቸው ድርጅቶች ወደ መንግስት ሲመጡ የሚሞላ መሆን እንዳለባቸው ገልፀው ይህ ድርጅት ጠያቂ፣ ሞጋች እና ማህበራዊ ኃላፊነቱን የሚወጣ ዜጋ በመቅረፅ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ስራ በመስራቱ ሉመሰገን ይገባል ሲሉ ገልፀዋል።